Friday, 19 May 2017

ፕላን B ን በአስቸኳይ እንጀምረው.!! የኔታ ሺህ ሞቱ እንኳን ቀረብዎ.!

Image may contain: 1 person, standing, horse and outdoor
የኔታ እና እኔ.! ቅዱስ ያሬድ ወደተሰወረበት ቅዱስ ያሬድ ገዳም ስንሄድ ለማስታወሻ የተነሳነው ፎቶ ነው ። እንዲህ በነፃነት በጉባኤ ቤታቸው ሚልዮን ተተኪ ሊቃውንት ማፍራት እየቻሉ የምን ሹመት የምን ጵጵስና ነው.??

ጎበዝ እንዳንዘናጋ !!
መተማመን እንደሁ
ውኃ በልቶታል
★ ★ ★
ይህ ጦማር በቀጣይ ሁላችንም ምን ማድረግ እንዳለብን እና እናንተም በምን ዙሪያ መዘጋጀት እንዳለባችሁ የሚጠቁም ጦማር ነው ።

✔የኔታ ዕዝራ ሀዲስ እንኳንም አልተመረጡ.! እንኳንም ቀረብዎ.!
✔ አንድነት እውነትም ኃይል ነው ።
✔ ውድ ጓደኞቼ የምን እጅ መስጠት ነው.!! የምን መብሰልሰል ነው አሁን ረጋ እንበልና፤ ቆም ብለን በማሰብ ፤ በጨዋ ደንብ በፍጥነት ወደ ፕላን B መንቀሳቀስ ነው ነው ያለብን ።
እመኑኝ.! ከምሬ ነው የምላችሁ መቼም በታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በዚህ ባሳለፍነው ወር ውስጥ ሃይማኖታችንን በተመለከተ ያደረግነው ትግል ለብዙዎች መልእክት ያስተላለፈ ነበር ። ዛሬ የአባ ኃይለማርያምና ፣ የአባ ተክለሃይማኖት መመረጥ ትንሽ ያበሳጨን ቢመስልም በጨዋታው ግን አሸናፊዎቹ እኛ ነበርን ።
ተመልከቱ በስልክ ጠሪ ብቻ ሆቴሎች ለግሪሳ ሁላ የመሰብሰቢያ አዳራሽ እንዲከለክል አደረግን ። ያውም ከአንድም ሦስት ኢንተርናሽናል ሆቴሎችን ይቅርታ አስጠይቀን ዝግጅት አስዘረዝን ። ይሄ ታላቅ ድል ነው ። አሰግድን የመሰለ አስቸጋሪ ግሪሳ እንዲወገዝ ታላቅ አስተዋፅኦ ያደረግነው እኛው ነን ። ይሄም ለእኛ ታላቅ ድል ነው ።
በዚህ ጉባኤ ምክንያት ብዙ ሰው ነቅቷል ፣ ተቀስቅሷል ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ በቤተክርስቲያን ላይ ፤ እየተደረገ ስላለው ደባና ሴራ እንኳን እኛ ኢትዮጵያውያን ይቅርና ፦
፩ኛ ፦ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሆኑ ቤተ እስራኤላውያንና
፪ኛ ፦ ሀገር ወዳድ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን በሚገባ ስለ ጉዳዩ አውቀዋል ።
፫ኛ፦ መንግሥትም የትግል ስልታችን አስደምሞታል ። ተኩሶ የሚገድለው የለ ፣ ቂሊንጦና ሸዋሮቢት ዝዋይና ቃሊቲ የሚያጉረው የለ ። ድንጋይ ውርወራ የለ ጎማ ማቃጠል የለ ። መጮህ መሰፏጨት የለ መፈክር ማሰማት የለ በቃ ስልክ ወጣ አድርጎ መደወል ። ተቃውሞውን በጨዋ ደንብ መንገር ። አለቀ በቃ ጉዳዩ እዚያ ላይ ይፈጸማል ። ይቆማል ። በቃ ይሄ መንገድ በጣም ተስማሚና አዋጭ ጉልበትና ጊዜም ቆጣቢ መንገድ ሆኖ አግኝተነዋልና ወደፊት ፋክስና ኤሚዬልን ጨምረን በቤተክርስቲያን ላይ የሚያላግጡትን በሙሉ ልክ እናስገባበታለን ። አከተመ ።
በሌላ በኩል በውጭው ሲኖዶስና በሀገር ቤቱ ሲኖዶስ ስር ተከፋፍለው ይገለገሉ የነበሩ ምእመናንና አንዱ ከአንዱ ጋር በጎሪጥ እንዲተያይ ሁለቱም የሃይማኖታችን ቁንጮና መሪ የሆኑ የእምነቱ መሪዎች በፈጠሩት ስህተት ምክንያት መሆኑን ኢትዮጵያውያኑ ከሚገባው በላይ በቂ ግንዛቤ ያገኙበትና የተለያዩ መግባባቶችም የተፈጠሩበትም ሆኖ አልፋል ። ይሄን የህዝብ ለህዝብ ግኑኝነት እንዴት እናስቀጥል የሚለው ነገር በሁላችሁም ዘንድ መታሰብ ይኖርበታል ። በቀጣይም ሁላችንም በደንብ እንመክርበትና በሁለቱም መካከል ያለውን ፀብ እናበርዳለን ፣ በሁለቱም ጠበኞች መካከል ያሉትን ግሪሳዎች በጋራ እናስወግዳለን ። የሁለቱም ፀብ የሃይማኖት ሳይሆን የሥልጣን ፣ የገንዘብ ፣ የዘር መሆኑን እናውቃለን ። ያውም የትግራይ ልጆችና የጎንደር ልጆች ጠብ ። አለቀ በቃ እውነቱ ይሄው ነው ። እሱን እንደምንም ብለን አብርደን የአንድ ሀገር ልጆችን ባይወዱም በግድ ማስታረቅ ይኖርብናል ። አንድ ስንሆን ነው የሚያምርብን ።
የሚገርመው በአሜሪካ የሚገኙት የተዋህዶ ልጆች በተ ከርስቲያን ሲሄዱ ተለያይተው ፣ ተኳርፈው ይሄዱና የቴዲ አፍሮ ኮንሰርት ሲሆን ግን በአንድ ክለብ ሄደው ኢትዮጵያ ሀገሬ እያሉ ሲያለቅሱ ይውላሉ ። በአመታዊው የእስፖርት በዓል ላይም ካሜራ ለማድመቅ ሲሉ በባንዲራ አሸብርቀው ሲያለቅሱ ፣ ሲደሰቱ ይከርሙና ልክ ቤተክርስቲያን ትዝ ስትላቸው መኳረፍ ይጀምራሉ ። እንግዲህ የሰባኪው ስብከት አንድ ማድረግ አቅቶት ቴዲ አፍሮ ከሆነ አንድ የሚያደርጋችሁ ወደ ፊት ቴዲ አፍሮን ሙሴ አድርገን መላክ አለብን ማለት ነው ። መቼም እንጨት እንጨት ከሚለው ከአሰግድ ስበከት የቴዲ አፍሮ ኢንተርቪ ለዘላለም ከአእምሮ አይጠፋም ። ያውም ከሚገርም የቋንቋ አጠቃቀም ጋር ።
በሌላ በኩል ተሃድሶ የለም ለሚሉና ለተሃድሶዎቹ ሳያውቁ ጥብቅና ይቆሙ ፣ ይከራከሩላቸው የነበሩ ወገኖችም አሁን ጨዋታው ፍንትው ብሎ ወጥቷል ። ታይቷልም ።
ሰሞኑን በጭንቀት ተውጠው የነበሩት ፕሮቴስታንቶችና ተሃድሶዎቹ በሙሉ ዛሬ በየብሎጋቸው ስሜታቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው ሲፈነጥዙ መታየታቸው በራሱ ለእኔ ታላቅ ድል ነው ። በአባ ኃይለማርያም እና በአባ ተክለሃይማኖት መሾም የጴንጤ መደሰት ነው እኔን ግራ የገባኝ ። " ተቃጠል ፣ አፈር ብላ ፣ አንተ አሳዳጅ ፣ እርር በል ያሉኝ ጴንጤዎች ብዛታቸው ። ቀይ ግን እነሱን ምን አገባቸው እና ነው እንዲህ ያስፈነጠዛቸው ያልን እንደሆነ መልሱ አለ ነገር ጠርጥር ከገንፎም ውስጥ አይጠፋም ስንጥር የሚለውን አባባል ያስታውሰኛል ። ምድረ ሰገጤ ሁላ.! ፓስተሮች ሳይቀሩ እኮ ነው የጻፉልኝ ፣ የደወሉልኝ ። እኔ ምን አገባኝ ታዲያ እንደ አመጣጣቸው አስተናግጄ መልሻቸዋለሁ።
ሁለቱ ተሿሚዎች ለእኔ በግሌ መልካም ወዳጆቼ ናቸው ። ለዚህም ነው አባ ተክሌ ስለፈሩኝ ወደ አሜሪካ በመደወል ለቀሲስ ንዋይ ካሳሁን እባክህ ዘመዴን ተወኝ በለው በማለት ለአማላጅነት ደጅ የጠኑት ። ፣ ዶር አባ ኃይለማርያምም ከአዲስ አበባ ድረስ ደውለው " ዘመዴ በእመቤቴ ፣ በቅድስት ሥላሴ ብለህ ተወኝ ፤ ያጠፋሁትም ነገር ካለ አስተካክላለሁ ። ከእነ በጋሻውም ጋር ሚሊኒየም አዳራሽ የተገኘሁት ታዝዤ ነው " እስኪሉኝና እስኪያለቃቅሱ ደረስ ያደረሰን የእኔ ድርቅናና ቅድሚያ ለሃይማኖቴ ማለቴ ነው ። እናም ዛሬም እኛ አሸንፈናል ። ጉባኤተኞቹን አስጨንቀናል ፣ አባቶቻችን ስህተት ቢሠሩም አስምጠናቸዋል ፣ ሹመቱ ቀድሞ ያለቀ እና የደቀቀ ፣ የተሿሚዎቹ መጽሔትም ቀደም ብሎ የተዘጋጀ ቢሆንም የግድ የጨነቀ ድራማ እነደዲሠሩ አስገድደናቸዋል ።
ሌላው በእኔ በኩል የየኔታ ዕዝራን መመረጥ ደግፌ አልነበረም እከራከር የነበረው ። ሁኔታው ክብረ ነክ መሆኑ ቢነደኝ ጊዜ ነበር እሪ የምል የነበረው ። በሃገሩ ሰው የሌለ ይመስል ኪዳን ማድረስ የማይችለውን ጓደኛዬን አባ ተክሌን ያለተወዳዳሪ አስቀምጦ ዐራት አይናውን ሊቅ ትምህርቱን በአግባቡ ካልጨረሰና አዘዞ ተወልዶና አድጎ ለስልጣንና ለሹመት ሲል አቡነ ጳውሎስ ትግሬ ነው የሚሾሙት የሚል ነገር በመስማቱ መታወቂያውን በአድዋ የቀየረን የስልጣን ጥመኛ ሰው ከእኚህ ታላቅ የሃገር አድባር ጋር ማወዳደሩ ተገቢ መስሎ ስላልታየኝ ነው ።
አባ ኃይለማርያም ከእኔ ወዳጅ ከብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ጋር ነው ቁርስ ምሳ እራት ማዕድ የሚቆርሱት ፣ አቡነ ጢሞቴዎስ ደግሞ እንኳን ጳጳስ ፓትሪያርክ በመምረጥ የሚታወቁና ሁሉን ማድረግ የሚችሉ አድራጊ ፈጣሪ ናቸው ። እናም የዶር መመረጥ የተበላ እቁብ መሆኑ ይታወቅ ነበር ።
የሚገርመው አረጋዊው አባት አቡነ ቀውስጦስ ሳት ብሏቸው የተናገሩትን ነገር እዚህ ጋ ማንሳት ይኖርብናል ። " ዕዝራ ጉበኤውን የት ጥሎ ነው ለጵጵስና የሚወዳደረው ፤ እኛ ዶርን ነው የምንመርጠው እሱን ነው የሚሻል " ብለው መናገራቸው እውነት ነው ። አቡነ ቀውስጦስ ዶክተሩን ይዘው በማኅበረ ቅዱሳን ጉባኤዎች ላይ እንዲሰብክ ይዘው መዞራቸው እና እንዲሰብኩ ማድረጋቸውም የገጽታ ግንባታ መሆኑ ነበር ።
አቡነ ቀውስጦስ ግን እውነት ነበራቸው ። ምክንያቱም የኔታ ዕዝራ ጳጳስ ቢሆኑ ጉባኤያቸው ይፈታል ። ቢሮ ይውላሉ ፣ ተተኪ ይጠፋል ፣ የተተኪዎች ምንጩ ይደርቃል ፣ እንደልባቸው መሆን አይችሉም ። በቁማር የጦዙ ፣ ሃይማኖት የሌላቸውን የአስተዳደር ሰራተኞች ሲዳኙ ነበር የሚውሉት ፣ የኔታ የቁም እስረኛም ይሆኑ ነበር ። የኔታ እኮ በበዓታቸው ተቀምጠው እያስተማሩ ፣ በርካታ ሊቀሊቃውንት ምሁራንን እያፈሩ ለቤተክርስቲያን የሚገብሩ ገባር ወንዝ እኮ ናቸው ። አሁን እንኳ በእንዲህ አይነት ትጋት እያስተማሩና እያገለገሉ በተጨማሪም በትርፍ ሰዓታቸው ደግሞ የሚገራርሙ ታላላቅ መጻሕፍቶችንም ለትውልዱና ለቅድስት ቤተክርስቲያን አበርክተዋል ። እና ምን በወጣቸውና ነው ጉባኤ ፈትተው የእግዚአብሔር መንፈስቅዱስን ትዕዛዝ ጥሶ በመንግሥት እየተጠመዘዘ ጳጳስ ከሚሾም የሲኖዶስ ጉባኤ ምን ይሠራሉ? ምንም አይሠሩም ። ሲኖዶሱ ቀረበት እንጂ እሳቸውማ ምን ሊቀርባቸው ። አረ በማርያም.!!
የዚህ ዘመን ጵጵስና እንደሆነ ብፁዕ አቡነ እንድሪያስን የመሰሉ ተጠያቂውን ፣ ታላቁን ሊቅ ሀገረ ስብከት አልቦ አድርጎ አስቀምጦ አስወግዶ የቁም እስረኛ ያህል በጠቅላይ ቤተክህነት ግቢ ታስረው እንዲቀመጡ ከማድረግ ውጪ ምን ጠቀማቸው ? ስንትና ስንት የቀለም ቀንድ የሆኑ ሊቃውንትን የሚያፈሩ አባት በጎሰቆለ ሁኔታ ፣ ለአንድ ሊቅ በማይገባ መልኩ ቤት ተዘግቶባቸው እንዲውሉ ከማድረግ ውጪ ምን ተጠቀሙ ? ምንም.?
በግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥትም ሆነ በደርግ ጊዜም ቢሆን የጳጳሳት ምርጫ የአገዛዞቹ እጅ ሳይኖርበት ቀርቶ አይደለም ። ያኔም ቢሆን የንጉሠ ነገሥቱን መልካም ፈቃድ ሳያገኙ የተሾሙ ጳጳሰት አልነበሩም ። ደርግም ቢሆን ፓትሪያርክ ያህል በገመድ አንቆ ገድሎ ነው የራሱን ፈቃድ የሚፈጽሙለት መነኮሳትን መርጦ የሾመው ። አቡነ ጳውሎስ ለ10 ዓመት በደርግ እስር ቤት ውስጥ የማቀቁት ደርግ ያለፈቃዴ ፣ እኔ ሳላምንበት ለምን ተሾሙ በማለት አኩርፎ ነው ያሰራቸው ። እንዲያም ሆኖ ግን የሚሾሙት ሊቃነ ጳጳሳት የዘመናዊ ትምህርት ዝግጅት በይኖራቸው እንኳ የቤተክህነቱን ትምህርት ጠንቅቀው የሚያውቁ ነበሩ ። የቤተክህነቱንም ሆነ ዘመናዊውንም ትምህርት ጠንቅቀው የዘለቁና ከሁሉም በላይ በሃይማኖታቸው አንቱ የተባሉና የተመሰከረላቸው ነበሩ ።
ፓትሪያርኩ አቡነ ተክለሃይማኖት በአንድ ቀን ታጭተው ፣ በአንድ ቀንም ተመርጠው ፓትሪያርክ ቢሆኑም ከተሾሙ በኋላ ግን ከመረጣቸው ደርግ ጋር እልህ በመጋባት ብዙ ሥራ የሠሩ አባት ነበሩ ። በረከታቸው ይደርብንና ቅዱስ ፓትርያርኩ ከጾም ብዛት አጥንታቸው ከሥጋቸው ተጣብቆ መሞታቸው ይታወቃል ። እንዲህ ነበር ያኔ ጵጵስና ።
አቡነ መርቆሬዎስም እድለኛ አልነበሩም ። የብሔራቸው ጉዳይ አንዱ ምክንያት መሆኑ እንዳለ ሆኖ ኢህአዴግ ፓትርያርኩን የሾማቸው ደርግ ነው በሚል ምክንያት ገፍቶና አሽቀንጥሮ ከመንበራቸው በማስወገድ የራሱን ሰው አምጥቶ አስቀምጦበታል ። ተመልከቱ ደርግ ፓትርያርክን ያህል ክቡር የሃይማኖት አባት አንቆ ሲገድል ህዝቡ ዝም ጭጭ በማለቱ ይህን የህዝብ ዝምታ በረሃ ሆነው የከታተሉ የነበሩት ህውሓቶች አጋጣሚውን አግኝተው ወደ ስልጣን ሲወጡ የመጀመሪያው እርምጃቸው ደርግ የፈጸመውን መፈጸም ነበርና ውሻ በቀደደው ጅቦቹ ገቡና አቡነ መርቆሬዎስን ከምንገድል ከምትሰደድ ብለው አጣብቂኝ ውስጥ በመክተት ከሀገራቸው እነዲሰደዱ አደረጉ ።
የአቡነ መርቆሬዎስን ከስልጣን መውረድ ተከትሎ ሥርዓቱ የራሱን ሰፈር ልጅ መሾም ይፈልግ ነበርና አቡነ ጳውሎስን ከተሰደዱበት ሀገረ አሜሪካን አምጥቶ 5ተኛው የኢትዮጵያ ፓትሪያርክ እንዲሆኖ ሾማቸው ። የአቡነ ጳውሎስ ዘመን አሁን በስልጣን ላይ ከሚገኙት ከአቡነ ማትያስ ጋር በጭራሽ በምንም መልኩ የማይገናኝ ፣ በፍጹም የተለየ እና የተሻለ እንደ ነበር አሁን ላይ ከሚታየው ነገር በመነሳት መመስከር ይቻላል። አቡነ ጳውሎስ እንደ ሀገር መሪ በወታደር ብዛት ታጅበው ለንግሥ በዓል መምጣታቸውን አግባብ አይደለም ብለን በወቅቱ ብንቃወምም አሁን ላይ ከምር የአባ ጳውሎስ እንዲያ መሆን ለእኔ ተናፋቂ ሆኖብኛል ። ( እኚህ እኮ ጭር ነው ያደረጉን )
ይባስ ብሎ አሁን የሚታየው ነገር ደግሞ ሲመለከቱትም ሆነ ሲያዩት እጅግ የሚያስጠላ ነው ። ሙሰኞች ቤተክርስቲያንን እንደ ግል ኩባንያ ቆጥረው እየዘረፉ ተምነሽነሸው የሚቀመጡባት ፣ ተጠያቂነት ድራሹ የጠፋባት ፣ ምንፍቅና ፣ ነውርና ነቀፌታ የበዛባን አገልጋይ ነን ባዮች እንደ አሸን የፈላንበት ዘመን ሆኗል የእኛ ዘመን ።
አሁን ለለውጥ መነሳት አለብን ። ቤተክርስቲያን የህዝብ ናት ። ያለ ህዝብ ቤተክርስቲያን ምንም ናት ። የቤተክርስቲያን ባለቤቷ ፣ አልባሿ ፣ ንዋያተ ቅዱሳቱን ፣ መጻሕፍቱን ፣ አስራቱንና በኩራቱን በሙሉ የሚያመጡት ምእመናን ናቸው ። በዚሁ ስሜት እጅግ ውስብስብ ቢሆንም እግዚአብሔርን አጋዥ አድርገን ለለውጥ እንነሳ ።
፩ኛ ፦ ከቅዱስ ፓትሪያርኩ ጀምሮ በቤተክርስቲያኒቱ የሥልጣን እርከን ላይ የሚገኙት ማናቸውም አባቶች ሊሰሩልን ፣ ሊባርኩን ፣ ሊቀድሱን ፣ ሊያፅናኑን የተሾሙብን እንጂ ሊሠሩቡን ፣ ሊነግዱብን ፣ ሊዋሹን ፣ ኢንቬስተር ሊሆኑብን ፣ ሊያስለቅሱን ፣ እንደ አንባገነን መንግሥታት በላያችን ላይ አይነኬ አይጠጌ ፣ ሆነው እንደፈለጉ ፣ እንዳሻቸው ሊፈነጩብን አይደለም ። ምእመናን ይህን በደንብ እንወቅ ። እናም እነሱ የሚሉንን እንደምንሰማቸው ሁሉ እነሱም የምንላቸውን ሊሰሙን ግድ ይላል ።
የማንፈልገውን ፣ የማናምነውን ፣ የምንጠራጠረውን ግለሰብ ለምን ይሾሙብናል ፣ እኮ ለምን??? ይሄ መታረም አለበት ፣የምናርመውም እኛው ነን ። እንዴት የሚለውን በቀጣይ እመለስበታለሁ ።
፪ኛ፦ በባንክ ፣ በውልና ማስረጃ ፣ በኢንሹራንስ ውስጥ የምትገኙ የተዋሕዶ ልጆች በሙሉ ። ከድሆች መቀነት ላይ ተፈትቶ ለቤተክርስቲያን አገልግሎት እና ልማት ይውል ዘንድ የተሰጡ ገንዘቦችን በጉልበታቸው በመዝረፍ ሀብት ያካበቱት ሌባ ጸሐፊዎች ፣ አለቆች ፣ ቁጥጥሮች፣ ገንዘብ ያዦች፣ የሀገረ ስብከትና የጠቅላይ ቤተክህነት ሹሞች እንዲሁም የጳጳሳት የገንዘብ መጠን ፣ የንብረት አይነት ፣ መኪና ፣ ቤት ወዘተ መዝግባችሁ ላኩልኝ ። ከዚያ ምን አይነት ውሳኔ እንደምንወስን አሳያችኋለሁ ።
24 ሰዓት በመቅደሱ ቆሞ በምስጋና በመጮህ እግዚአብሔርን የሚያመሰግነው ፣ ምእመናንን በኪዳን ፣ በቅዳሴ ፣ በማኅሌት ፣ በክርስትና ፣ በኃዘን በደስታ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል እንደመላእክት የሚያገለግለው ምስኪኑ የልጆች አባት የሆነው ካህን በሰቀቀን ይኖራል ። እሱ ባገለገለው አገልግሎት ምክንያት የመጣውን ገንዘብ ግን የሚበላው ፊደል ያልቆጠረ እና በጉቦ የተሾመ ተራ ካድሬና መሃይም እልም ያለ ሰገጤ በላተኛ ነው ። እናም የካህናትን መብት እኛው ልጆቻቸው እናስከብርላቸዋለን ። እመኑኝ ይህን ለማድረግ ጊዜው ሩቅ አይደለም ።
ምድረ ስግብግብና ሆዳም ከድሬና ዘራፊ ሁላ መንግሥቱ የሥጋ ዘመዶቹ ፣ የሥራ ባልደረቦቹ እና የጥቅም ተካፋዮቹ ስለሆኑ ህግ እንዳይነካቸው ፣ እንደይጠየቁ ፣ እንዳይከሰሱ ፣ ባልተጻፈ ህግ ፈላጭ ቆራጭ ሆነው ተንደላቅቀውና ምንም ሳይጎድልባቸው በሙዳየ ምጽዋት ገንዘብ የሀረር ሰንጋ መስለው ዘና ፈታ ብለው እንዲቀመጡ ያደረጋቸውን የቀን ጅቦች በሙሉ እናስተፋቸዋለን ። የቤተክርስቲያንን ገንዘብ አይናችን እያየ እንመስመልሰዋለን ። ይሄ ደግሞ መብት ነው። ድንጋይ መወርወር ፣ ድምጽ አውጥቶ መጮህ ፣ ማፏጨት ፣ ኡኡ ማለት አያስፈልግም እንዲያው በዝምታ ፣ እንዲያው በትእግስት ፍጥምጥም ማድረግ ይቻላል ። ይኽን ፓትሪያርኩ በሸገር ሬድዮ ቀርበው አስቸጋሪ ነው ያሉትን ሙሰኛ ሁላ አስቸጋሪነቱን እንፈትሸዋለን ፣ ቡሩስሊ ይሁኑ ሸዋዚንገር እስቲ እናያቸዋለን ። ፌደራል ፖሊስ ከሌባ ጋር እንደሚቆምም እናያለን ።
፫ኛ ፦ እንደ አቡነ ማርቆስና ዶር አባ ኃይለማርያም ያሉ ሰዎች ከእነ በጋሻውና ያሬድ አደመ ፣ የፊደል ሬስቶራንት ባለቤት ከሆነው ከአቶ ኤፍሬም ጋር በመሆን በቅድስት ቤተክርስቲያን ስም የሰበሰቡትን ብር አይናችን እያየ በ53 ሚልየን ብር የከፈቱትን ፋብሪካ ለቤተክርስቲያን እንዲመለስ እናደርገዋለን ። ዶር አባ ኃይለማርያም ገንዘቡን ይዘው ልጆቹ ጠፍተዋል ቢሉም አቡነ ማርቆስ ግን ተካፋይ እንደ ነበሩ ማስረጃዎች አሉ ። እናም ቱ ምናለ በሉኝ የበሏትን በሙሉ እናስተፋለን ።
፫ኛ ፦ ከዛሬ ጀምሮ የመነኮሳትን ልብስ መብሶ በየቡና ቤቶቹ ውስጥ የሚንዘላዘል ዘልዛላ አሰዳቢ ሰካራምና ዘማዊ መነኩሴ ፣ ከህን እና ዲያቆን ካገኛችሁ እነዚህን አሰዳቢ ወራዶች የመጠየቅ ፣ ምንትሠራለህ ብሎ የመሞገት መብት አላችሁ እናም ሰፈራችሁን አሰከብሩ ። ከዚያ ከባሰበትና ከፈነዳ አውልቆ ህዝባዊ ይሁን እንጂ በማንም ለከርሱ ሲል በመነኮሰ ሆዳም መነኩሴ የተነሳ የአባ እንጦንስና የአባ መቃርስ አስኬማ አይዋረድም ። አራት ነጥብ ።
እንግዲህ ከእኛ የሚጠበቀው ምንድነው ያላችሁ እንደሆን ይህን መልእክት የምታነቡ ምእመናን በሙሉ ። በመጀመሪያ በምንገኝበት አጥቢያ በመሄድ የንስሀ አባት እንያዝ ፣ ንስሐም እንግባ ፣ ቀጥሎ መብትን ለመጠየቅ ግዴታ መግባት ያስፈልጋልና በአስቸኳይ የሰበካ ጉባኤ አባል እንሁን ። የሚጠበቅብንን ክፍያም አሟልተን በደብራችን የሰበካ ጉባኤ የአባልነት መታወቂያ እንያዝ ። ክፍያው በጣም ትንሽ ነው ። ያንጊዜ መብት ይኖረናል ። የፈለግነውን ጥያቄ መጠየቅም እንችላለን ። ይሄን ሳይውል ሳያድር ፈጽሙት ።
፬ኛ፦ ወጣቶች በአስቸኳይ ወደ ሰንበት ትምህርት ቤት ግቡ ። ተማሩ ፣ ዘምሩ ። አገልግሉ ። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በማኅበረ ቅዱሳን በሚዘጋጀው የግቢ ጉባኤ በመሳተፍ የድርሻችሁን ተወጡ ። የፖለቲካውን ስፍራ አትፍሩት ። ጠጋ በሉት ። ያዙት ። አለቀ ።
እኔ እንዲህ ነው የማስበው ፣ እንዲህ ነው የምመኘው ። አባ ኃይለማርያም ተሾሙ አልተሾሙ አሁን እሱ ላይ እኝኝ ስንል መገኘት የለብንም ። ይህ ሰው መንግሥት አሁንም ላሹመው ካለ ከልካይ የለበትም ። ቢሾምስ ጎንደር ሊሄድ ነው? ማንስ ክህነቱን ያረከሰ ጳጳስ መስቀል ይሳለማል ። ያው ፓርላማ አስገብቶ ቢሮ ካላሰራው በቀር መቼም በህይወት እያለን የሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ አይሆናትም ። ቱ ሞተናታላ ።
አባ ተክለ ሃይማኖትም ቢሆን እኔም ቢሾም ጉዳዬ አልነበረም። ከመሾሙ አይደለም ተቃውሞዬ ። እሱ ግን ውሎው ከእነ በጋሻው ፣ ከእነ መናፍቁ አስራት አያንሳ ጋር ነው። በኮሌጅ አብረው የተማሩትን ኦርቶዶክሳውያን ልጆች መች በአውደምህረቱ ላይ አቁሞ ያውቃል.?? መቱ ከመምህር ምህረተአብ ጋር አፈር ፈጭቶ ያደገው ፣ በሰንበት ትምህርት ቤትም ሲያገለግል የነበረው አባ ተክለሃይማኖት ከመናፍቃኑ ግሪሳዎች ጋር እልም ያለ ፍቅር ውስጥ ወፍቆ ሲዳክር እናይ የለ እንዴ ። 6 አባወራዎች በሚገኙበት ቦታ ሁሉ ቤተክርስቲያን ካልከፈትኩ ማለትና ካህንና አገልግሎት የማይሰጡ ሲቪ ማሳመሪያ ቁጥር ብቻ የሆኑ አብያተክርስቲያናትን መክፈቱ ብቻውን በቂ አይደለም ። እናም በመንግስት ደብዳቤ በግድ የተሾሙት ጳጳስ ካቢኔውን ይባርኩ ካልሆነ በቀር ምን እነደሚሠሩ እናያለን ። ይልቅ መንግሥት ለምን ሰውየው እንዲሾሙለት እንደፈለገ ካስፈለገ ለማውጣት እገደዳለሁ ። እናም በአስቸኳይ ማስተካከያ ይደረግበት ።
በተረፈ ሊቀሊቃውንት የኔታ እዝራ ሀዲስ ፣ እንኳን ደስስ ያሎት ። እንደኔ እንደኔ ሹመቱ አሁን እንደምናየው ሌሎቹም የተሾሙቱ በቀደመው መንገድ በአግባቡ ሥራ ላይ ሲያውሉት አይታይምና እንደኔ እንደኔ ሹመቱ ለእርስዎ ሺህ ሞት ነውና ቢቀርቦት ባይ ነኝ ። ይተውት ፣ ይናቁት ። እነሱ እርስዎን ለማዋረድ እንደደከሙት እርስዎ ደግሞ በተለመደው ፈገግታው ባላየና ባልሰማ ይለፏቸው ። ኪዳን ማድረስ ከማይችለውና ለፖለቲካ መጠቀሚያነት መንግሥት ታንክ አቁሞ ካስመረጠው ከጨዋው አባተክሌ ጋርማ እርስዎ እኩል ብፁዕ አባታችን ተብለው አይጠሩም ። እርስዎ ክብርዎ ከምን እንደሆነ የምናውቅ እናውቀዋለን ። አከተመ ።
ስደተኛውና ሀገር አልባው አክባሪ ልጅዎ
እንኳንም ተሰደድኩ ፣ እንኳንም አስጨንቀው ከሀገሬ አስቀሩኝ ። ስለእውነት እንነጋገር ከተባለ አሁን እንደምፈነጨው በሀገሬ ብሆን እፈነጭ ነበርን? ። መንፈራገጤ አይቀርም ነበር ። ነገር ግን ኮማንድ ፖስቱ ዋጋዬን ሰጥቶ አደብ ያስገዛኝ ነበር ። ወይ አንቀጽ ጠቅሶ ሸዋሮቢት ፣ ወይ ደግሞ አከናንቦ ሰማይ ቤት ይልከኝ ነበር ። አሁን ግን ለጊዜው ሰላም ወረዳ ነው ያለሁት ፤ እናንተ መረጃዎችን ላኩልኝ እኔ እንደሚሆን እንደሚሆን አደርገዋለሁ። እስከ ጊዜው ድረስ ።
" እኔ ግን እላለሁ !!! እምዬ ኦርቶዶክስ አንቺ እናትዓለም ፤ የእነ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ፣ የእነ ቅዱስ አትናቴዎስ እና ቅዱስ ቄርሎስ የእነ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ የእነ ቅድስት አርሴማ ፣ የእነ አቡነ ተክለሃይማኖት ፣ የእነ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ፣ የአባ ሳሙኤል ዘዋልድባና የአቡነ አረጋዊ ሃይማኖታቸው የሆንሽ ንጽህት ተዋሕዶ ሃይማኖቴ ሆይ ! ብረሳሽና ብከዳሽ ቀኜም ትርሳኝ፣ ትክዳኝም ። ባላስብሽና ባልሞትልሽ ምላሴ ከጉሮሮዬ ይጣበቅ ። ሳለጎበድድ ሳለከዳሽ እንድኖር አምላክሽ ይርዳኝ ። ይህን ባለደርግና ሳልጮህልሽ ዝም ብዬ ብሞት ስሜ ከህይወት መጽሐፍ ይደምሰስ ።
አንቺ ቅድስት ቤተክርስቲያን ሆይ.! ጌታ በደሙ የመሰረተሽ ነሽና ደሙ ይፍረድልሽ ። አከተመ በቃ.!
"ጌታ ሆይ! ከዚህ በፊት በሆነው ፤ አሁንም እየሆነ ባለው ነገር እና ወደፊትም በሚሆነው ነገር ፤ ክብሩን ሁሉ አንተ ውሰድ ።" አሜን. !
"ድንግል ሆይ እናቴ ! አዛኝቱ ዛሬም እንደትናንቱ ቅደሚ ከፊት ከኋላዬ "
ፌስ ቡክ What's on your mind? ስላለኝ ይህንንም ራሴው ከአእምሮዬ አቅንቼ በእጄ ጻፍኩት ። +4915217428134 የቫይበር ፣ የኢሞና የኋትስአፕ መልእክቶችን የምቀበልበት የእጅ ስልኬ ነው ።
ሻሎም.! ሰላም.!
ዘመድኩን በቀለ ነኝ።
ግንቦት 11/2009 ዓም
ከራየን ወንዝ ማዶ።

No comments:

Post a Comment

አዝማሪ ትዝታው የራሱንና የቤተሰቡን የአንገት ማዕተብ ከበጠሰ ቆየ ።

ግሪሳ ትዝታው ( ሉንጎ )  መቅሰፍት ሊወርድበት  ነው ★ ★ ★ ✔  Share ~ Comment ~ Like ~ Tag ★ አዝማሪ ትዝታው የራሱንና የቤተሰቡን የአንገት ማዕተብ ከበጠሰ ቆየ ። ★በኮሎራዶ.! ...